yooyaapress.com
info @yooyaapress.com

ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

audit, report, verification-4576720.jpg

ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

በባለሥልጣኑ የተሽከርካሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በድሉ ሌሊሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሕገወጥነትን ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ አንዱ ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ መኪናዎችን የመለየት ሥራ አንዱ ነው። ይህም ከተጀመረ አንድ ወር ሆኖታል።

‹‹ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ባደረገው ጥናት በባለሥልጣኑ የሚመዘገበው የገንዘብ መጠን እና ለገቢዎች ቢሮ የሚቆረጠው ደረሰኝ ተመሳሳይ ያለመሆን ሁኔታዎች አሉ። በዚህም በተለይ የአዲስ ተሽከርካሪዎች ዋጋ የሚቆረጥበት ደረሰኝና ገዢዎች ለመኪናው የሚከፍሉት ዋጋ ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡›› ብለዋል።

በዚህም መንግሥት ከተሽከርካሪዎች ግዥና ሽያጭ ማግኘት የሚገባውን የታክስ ገቢ እያገኘ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ መኪናዎችን የመለየት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

‹‹ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ኹለት አይነት ሕገወጥ ተግባራት ይገጥሙታል›› ያሉት ኃላፊው፤ እነሱም ከክልል በዝውውር የሚመጡ መኪናዎች ላይ እና በተጭበረበረ ሰነድ የተመዘገቡ መኪናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ይህንን ለመከላከል የሚያግዝ ዘመናዊ ሥርዓት የመኪናዎቹን ሕጋዊነት የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ይህም የማጣራት ሥራው የሚሠራው ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ ነው፡፡›› ያሉት በድሉ፤ ከዚህ በፊት አንድ የመኪና ሻጭ በሥሙ የነበረውን መኪና ለሌላ ሰው ሲያስተላልፍ የማጣራት ሥራ እንዳልተሠራ በመግለጽ፤ ‹‹በዚህም መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ታክስ አላገኘም። አሁን ግን ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን አዲስ ሥርዓት መዘርጋት ተችሏል፡፡›› ብለዋል።

‹‹ሥርዓቱም መንግሥት ከተሽከርካሪዎች ማግኘት የሚገባውን ታክስ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ መኪና ገዢዎች እንዳይጭበረበሩ እና መንግሥት ሕገወጥነትን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት የሚያጠናክር ነው። በሂደቱም በሕገወጥ መንገድ የገቡ መኪናዎች የሚወረሱ ይሆናል፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም፤ ‹‹የአዲስ መኪና ገዢዎች የሚከፍሉት ዋጋ በደረሰኙ ላይ መጠቀሱን በማረጋገጥ ሊገዙ ይገባል። ይህንን ማድረግ ለገዢው በርካታ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ከመሆኑ ባለፈ የሚሰበሰበው ገቢ ለከተማዋ መሠረተ ልማት የሚውል በመሆኑ በኃላፊነት ሊታይ ይገባል›› ሲሉም ተናግረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *