yooyaapress.com
info @yooyaapress.com

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በመንግሥት ዉስጥ ሆነው ሕዝብንና መንግሥትን የሚያጋጩ አካላት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጥሪ አቀረበ

Ethiopia court

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መንግሥት ኢስላም ጠል የሆኑ እና በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ በተለያዩ እርከኖች ያሉትን አካላት በመገምገም እና በማጥራት ሕዝብንና መንግሥትን ሆነ ብለው ለማጋጨትና አገሪቷን ወደ ለየለት ቀውስ ለመውሰድ እየሰሩ ያሉ አካላትን ፈትሾ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ መዋቅሩን እንዲያጠራ ጥሪ አቀረበ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ትናንት ግንቦት 18/2015 በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ በአዲሱ ሸገር ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ የሚገኘውን የመስጂዶች ፈረሳ እንዲቆም ለማሳሰብ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ፤ በዛሬው ዕለት በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ የምክክር ጉባኤ ባለ አስራአንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያወጣው አቋም መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እኛ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በግንቦት 19/2015 በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ የምክክር ጉባኤ ላይ የተሳተፍን የጠቅላላ ጉባኤ አባላት፥ የዑለማ ምክር ቤት እና የክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት አባላት በወቅታዊ የህዝበ ሙስሊሙ ጉዳዮች ላይ ባደረግነው ምክክር የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

1. በሸገር ከተማ እየተደረገ ካለው የመስጂድ ፈረሳ ሂደትን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በአንዋርና ኑር መስጊዶች ዙሪያ የመስጂድ ፈረሳውን በሚቃወሙ ሙስሊሞች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ንጹኃን ሙስሊሞች አላህ በሸሂድነት(ሰማዕትነት) እንዲቀበላቸው፥ ለቤተሰባቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን አላህ እንዲሰጣቸው እንማጸነዋለን። በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን  በቶሎ መሻርን አላህ እንዲለግሳቸው እንማጸነዋለን።

2. በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በአንዋርና ኑር መስጊድ የተፈጠረው ክስተት እንዴት እንደተፈጠረና የደረሰውን ሞትና ጉዳት መንስኤዎች የሚያጣራ ከመንግሥትና የእስልምና ጉዳይ ም/ቤት በጋራ ያሉበት ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በአስቸኳይ እንዲቋቋም እንጠይቃለን።

3. በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሸገር ከተማ ኢስላምንና ሙስሊሞችን በናቀ መልኩ በመስጂዶች ላይ እየተደረገ ያለው የጅምላ ፈረሳ ሂደት በአስቸኳይ እንዲቆም፥ እንዲሁም ለፈረሱት መስጊዶች የክልሉ መንግስት ምትክ ቦታ በመስጠት በአስቸኳይ ተመልሰው እንዲገነቡ በማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ እንዲክስ እናሳስባለን።

4. በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገራችን ክልሎች ለእምነት ቦታዎች ተገቢውን ክብርና ጥበቃ እንዲደረግ፥ እንዲሁም ለመስጂዶች ካርታ በመከልከልና ሆነ ብሎ ቢሮክራሲውን በማንዛዛት ሕዝቡን ላማረሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መንግስት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በአፋጣኝ እንዲፈታቸው እናሳስባለን።

5. በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጣቸው የእምነት ነጻነትን በመጻረር በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች በተለይም በጉራጌ ዞን በጉንችሬ ሙስሊም ተማሪዎችን ለይቶ ከትምህርት የማባረር ሂደት በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጠበት። መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በኢስላም ጠልነት ምክንያት በሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በዘላቂነት የሚያስቀርና ለሃይማኖታዊ መብቶቻችንን የሚጥሱ አካላትን የሚቀጣ ሕግን መንግስት እንዲያወጣ እንጠይቃለን።

6. ሕዝበ ሙስሊሙ ከመሪ ተቋሙ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ጎን በመቆም ሃይማኖታዊ መብቶችን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።

7. የሃይማኖታችንን ክብር ብሎም የአላህ ቤት የሆነውን መስጂድ መድፈርና ማዋረድ እጅግ ዉስጥን የሚያደማ ብሎም ስሜታዊ የሚያደርግ መሆኑን የመንግስት የጸጥታ አካላት በመገንዘብ ወደ ሕብረተሰቡ ከመተኮስ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

8.ሕዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄዎቹን ለማስከበር ከመሪ ተቋሙ መጅሊስ ጎን በመቆም በሚያደርገው ህጋዊ ትግል ለራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ሕዝበ ሙስሊሙን መረማመጃና መጠቀሚያ ሊያደርጉ ከሚችሉ አካላት የማባባስና ግጭትን የማስፋፋት ቅስቀሳና ሴራ ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ እናደርጋለን።

9.የሕዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄዎች የምናስከብረው በአንድነትና በመደማመጥ በመቆም ሕዝበ ሙስሊሙ በየእርከኑ ካሉ የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤቶች ጎን በመቆም አንድነቱን በማጠናከር ለመብቱ ትግል ስኬት በአንድነት እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን።

10. መንግሥት ኢስላም ጠል የሆኑ እና በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ በተለያዩ እርከኖች ያሉትን አካላት በመገምገም እና በማጥራት ሕዝብንና መንግሥትን ሆነ ብለው ለማጋጨትና አገራችንን ወደ ለየለት ቀውስ ለመውሰድ እየሰሩ ያሉ አካላትን ፈትሾ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ መዋቅሩን እንዲያጠራ ጥሪ እናደርጋለን።

11. በአገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ሕዝበ ሙስሊሙ በንቃትና በስፋት በመሳተፍ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ የሕዝበ ሙስሊሙ ችግሮችን፥ ጥያቄዎችንና አጀንዳዎችን በማንሳት ኹሉንም ኢትዮጵያውያንን በፍትሃዊነትና በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለመግንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *